• Call Us
  • +25146 2206572

ኢመደኤ እና ከደቡብ ክልል የሳይንስ፣ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፡ 19/01/2014፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ እና የደቡብ ክልል የሳይንስ፣ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ በኢመደኤ በኩል የተገኙት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ ኢመደኤ በዘርፉ ትልቅ አቅም እንደለው ገለጸው የደቡብ ክልል የሳይንስ፣ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮም ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም እና የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ከኢመደኤ ጋር በጋራ ለመስራት መወሰኑን አድንቀዋል፡፡

በቀጣይም ቢሮው ደህንነቱ የተጠበቀ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለመዘርጋት በሚያደርገው ጥረት ኢመደኤ የበኩሉን ኃላፊነት ይወጣል ሲሊ ዶ/ር አንተነህ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል የሳይንስ፣ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ በበኩላቸው መ/ቤታቸው ቀደም ሲልም ከኢመደኤ ጋር በሳይበር ደህንነት ዙሪያ በጋራ ሲሰሩ እንደነበር አውስተው የዛሬው ስምምነትም ይበልጥ ተቋማቸው ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ አሰራር ለመጠቀምና የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል፡፡

በኢመደኤ ሳይበር ቢዝነስ ልማት ማዕከል ኃላፊ አቶ ሄኖክ አዱኛ ስምምነቱ በሳይበር ደህንነት ግንዛቤ መፍጠር፤ የቢሮውን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች ላይ የኦዲት ስራ ማከናወን፤ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት፤ የድህንነት ፖሊሲ መገምገምና ማሻሻል ላይ ያተኮረ መሆኑን በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡