• Call Us
  • +25146 2206572

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታት ወጣቶች ችግር ጠቋሚ ሳይሆኑ የአካባቢያቸውን ችግር ፈቺ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

በሳይንስና ተክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ስራ የሚሞክሩትን ስናበረታታ የሚችሉ ይፈጠራሉ በሚል መሪ ቃል የዲላ ዩኒቨርስቲ እስቴም ማዕከል ከጌዴኦ ዞን ትምህር መምሪያ እና ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ጋር በመተባበር የፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽንና ፓናል ውይይት በዲላ ከተማ አካሂዷል።

በመርሃ-ግብሩ የተገኙ የደቡብ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሳይንስ ፈጠራ ስርጸት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሂዲን ሁሴን ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻሉባቸው በቂና ምቹ የሆነ ምህዳር መፍጠር ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቅ እንደሆነና ሳይንስና ተክኖሎጂ በዘላቂነት ውጤታማ ሆኖ እንድቀጥል የተጠናከረ እውቀትና ዝንባለ ያለውን ትውልድ መፍጠር እንደምያስፈልግ ተናግረዋል።

ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሁሉለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊ በዘርፉ ለተጠቃሚዎች ዕድገት ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ በሚገባ ለመጠቀም የሚያስችሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን ለማሳደግ የሚያግዙ እቅዶች ተግባራዊ እንድሆኑ ጠይቀዋል፡፡

የፈጠራ ስራዎችን በትምህርት ቤት ደረጃ በስፋት እንዲተገበር መደገፍና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው ሁሉም የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል።

በኤግዚቢሽኑ የሳይንስ ክበባት አመራርና ሱፐርቫይዘሮችን የፈጠራ ስራን ባህል ለማጎልበትና በሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች የተማሪዎችን ፍላጎት ለማነሳሳት የፈጠራ ስራ እንዲሰሩ ሊያደርጉ የሚችሉ ስራዎች ለተማሪዎች እይታ ቀርበዋል፡፡

የዞኑ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብነት አክሊሉ የተማሪዎች የፈጠራ ስራ እንዲዳብር ከማድረግ አንፃር በተለይም መምህራንና ወላጆች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ በመጠየቅ ተማሪዎች ተሰጥኦና የፈጠራ ስራ እንዲያጎለብቱ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም በትምህርት ቤቶች የተለያዩ ፈጠራ ስራዎችን የሚሰሩ ተማሪዎችን በማበረታታት ሀገራችን ኢትዮጵያ በተክኖሎጂ ዘርፍ ውጤታማ እንድትሆን ትኩረት ተሰጥቶ እንደምሰራ መናገራቸውን የዘገበው የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ነው።