ቴክኖሎጂ ለአንድ ሃገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከምንም በላይ መሆኑን ዛሬ ላይ የስልጣኔ ጫፍ የደረሱ ፣ የበለፀጉና የዓለማችን ሃያላን ተብለው የሚጠሩ አገሮች ምሥክሮች ናቸው፡፡ይህም በመሆኑ መንግሥት የሃገራችን ሕዝብ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆንና የቴክኖሎጂው ሽግግር ከጫፍ እንዲደርስ ተግቶ በመሥራቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀላል የማይባል የሃገራችን ሕዝብ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን ችሏል፡፡ ለዚህም ማሳያ መሆን የሚችሉ በርካታ ተግባራትን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን በክልላችን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከሚመለከታቸው መ/ቤቶች ጋር በመሆን በአያሌ የገጠር ቀበሌያትና ወረዳዎች የገጠሩ ሕብረተሰብ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከሌሎች የመረጃ ምንጮች የሚፈልጓቸውን መረጃዎች በተለያዩ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች አማካይነት ማግኘት እንዲችሉ የማህበረሰብ መረጃ ማዕከላትን አቋቁሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሽቦ አልባ ስልኮችም በብዙ የገጠር ቀበሌያት በቢሮው አግባብነት ባላቸው ተቋማት በኩል የተሠራጩ ሲሆን እስኩል ኔትና ወረዳ ኔቶችም እንዲሁ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንዲሁም በያዝነውም በጀት ዓመት በክልል ማዕከል ፣ በዞኖችና በወረዳዎች የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ደረጃ በደረጃ እየተዘረጋ ያለ ሲሆን በዋናነት የመንግስት መረጃ ሥርዓት የማሳለጥ፣ የቪዲዮ ኮንፍረንስ አገልግሎት በመስጠት ፈጣን የሆነ መረጃ እንዲዳረስ የማድረግና የማህበረሰብ መረጃና ሬድዮ አገልግሎት በመስጠት በርካታ ወጣቶችን በማደራጀትና በማሰልጠን ወደ ስራ እያስገባ ይገኛል፡፡በኢኮቴ ዘርፍ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተመራቂዎችን በማህበር በማደራጀት ለሁለት ዓመታት የተለያዩ ድጋፎችን ማለትም ስልጠና፣ የገበያ ማፈላለግና የማማከር አገልግሎት በመስጠት የግል ካምፓኒ ፈጥረው ወደንግድ ዓለም እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቢሮውን ዌብ ሳይት በማልማት እና የፌስቡክ ገጽ በመክፈት ለመላው የዓለማችን ህብረተሰብ የተለያዩ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እተከናወነ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ቢሮው ከክልል እስከ ወረዳ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ከመዘርጋት፣ ከማስፋፋትና ክህሎትን ከማዳበር አንፃር ያከናወናቸው አበረታች ተግባራት ቀጣይነት እንዲኖራቸው ባለድርሻ አካላት ዘርፉ በክልላችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲበለጽግና ሕዝባዊ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል፡፡
ስለዚህ በክልላችን የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ት/ቤቶች፣ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች በሙሉ ሃገራችን አድጋ ወደ ታቀደው ስፍራ ለመድረስ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ተገንዝበው ጥያቄዎችን በራስ ተነሳሽነት በማቅረብ እና ከቢሮው ጋር በቅርበት በመስራት የታቀደው ግብ ላይ ለመድረስ የበኩላችንን እንድንወጣ ከአደራ ጭምር አሣስባለሁ፡፡
Copyrights 2020. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SCIENCE AND INFORMATION TECHNOLOGY BUREAU